ተወልዳ ያደገችው እንጅባራ ወረዳ ገበሬ ማህበር ሲሆን የተወለደችውም ከድሃ ቤተሰብ ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባ የመጣችው ህይወቷን ቀይራ ቤተሰቧን ለመርዳት አስባ በጉልበት ሥራ ወይም በቤት ሰራተኛነት ሥራ ለመቀጠርና ገቢ ለማግኘት ተስፋ በማድረግ ነው፡፡ ከዚያ መጀመሪያ የቤት ሰራተኛ ሆና መሥራት ጀመረች ፡፡ ከዚ,ያም ባገኘችው የተሻለ ዕድል የሆቴል ቤት ጽዳት መሥራት ቀጠለች በዚያም ቆይታዋ የምግብ አብሳይ ረዳት ሆና መሥራት ቀጠለች ደመወዟም በመጠኑ አደገላት ተስፋዋ እየጨመረ ሄደ፡፡ በዚያን ጊዜ ነበር ከሃና አባት ከአብርሀም ጋር ግንኙነት የጀመረችው፡፡ አብረው እንደሚኖሩና እንደሚያገባት አሳምኗት ለ8 ወራት ያህል አብረው ኖሩ በዚህ ጊዜ ሃናን እርጉዝ መሆኗን አወቀች ይህንን ለአብርሐም በነገረችው ጊዜ በድንገት በወጣበት ቀረ፡ ጥሏት ጠፋ፡፡ ብታፈላልገውም ልታገኘው ስላልቻለች ኑሮዋን በራሷ ለመቋቋም የምትችውን እየሠራች ለመቀጠል ቆርጣ ተነሳች፡፡ ወርቄ እስክትወልድ ድረስ የቻለችውን ያህል እየሠራች ለእለት ኑሮዋ በመሸፈን ለቤት ኪራይ ትከፍል ነበር፡፡ ሃናን ከወለደች በኋላ ግን እንደ በፊቱ ሥራ ሊሆንላት አልቻለም፡፡ እራሷን ለመርዳት ያገኘችውን ማንኛውንም ነገር ለመስራት ሞከረች ነገር ግን ከልጅዋ ጋር እሷን ለመቀጠር ፈቃደኛ የሆነ ማንም የለም ፡፡ ከየትኛውም ጊዜ ይልቅ ችግሩ ጠናባት፡፡ ያለ ሥራ ያለሰው ድጋፍ መኖር የማይታሰብ ነገር ነው፡፡ እሷም ልጇም የሚበሉት እስኪያጡ ተራቡ፡፡ ቤት አልባ እና ተስፋ የቆረጠች ሆና ከህፃን ሃና ጋር ሕይወት ለማስቀጠል ወደ ልመና ለመሄድ ተገደደች ፡፡
ለ1ዓመት ከ4 ወር ያህል ቤት አልባ ሆና ቀምሶ ለማደር ያህል በየመንገዱ በየቤተክርስቲያኑ በመቀመጥ እርዳታ በመጠየቅ አሳለፈች፡፡ ከዚህ በኋላ ፍቅር ለሕጻናትና ለእናቶች በጎ አድራጎት ድርጅት ባለው ክፍተት የድሃ ድሃን ለመቀበል ዝግጅቱን ጨርሶ ስለነበር አወዳድሮ ከተቀበላቸው ችገረኞች አንዷ ወርቄ ነበረች፡፡ የሚያስፈልገውን ሂደት ከጨረሰ በኋላ በፍቅር ለህፃናት እና ለእናቶች በጎ አድራጎት ወርቄና ልጇ ሃና ሙሉ እርዳታ ማግኘት ጀመሩ፡፡
ከሚያገኙትም አገልግልቶች፣
- ሃና፡ ንፅህናው በተጠበቀ ሁኔታ በሕፃናት መዋያ ውስጥ መዋል፣ በቀን ሦስት ጊዜ ትኩስና ተመጣጣኝ ምግብ መመገብ ፣ የልብስና የጫማ ስጦታ፤ የሕክምና አገልግሎት በነፃ ታገኛለች፣ በዴኬር ፕሮግራም መሠረት የጨዋታ ጊዜ የእንቅልፍ ጊዜ የሙዚቃ ጊዜ ጨምሮ ለዕድሜዋ የሚሆን የመጀመሪያ የትምህርት ልምምድ ይሰጣታል፡፡
- ወርቄ፡ ልዩ ልዩ የህይወት ክህሎትን ፡- የስነ ልቦና ድጋፍ፤ የግልና የአካባቢንጽህና፣ ከሰዎች ጋር መልካም ግንኙነት፣ የቤተሰብ ዕቅድ፣ የመጀመሪያ እርዳታ፣ የሥራ ፈጠራ ሥልጠና፤ የባንክ አካውንት አከፋፈትና የገንዘብ ቁጠባ ሥልጠና ወስዳለች፡፡ በመቀጠልም በፊት ትሠራ የነበረውን የምግብ ማብሰል ሥራ ለመሥራት የሚያስፈልገውን እቃዎች የምትገዛበት የዘር ብር አቅርቦትና አቅም በፈቀደ የልብስና የጫማ ድገፍም አድርጎላት ወደሥራ ገብታለች፡፡ ወርቄ ልጇ በዴይኬር በጥሩ ሁኔታ ስለተያዘችላት በጣም ደስተኛ ከመሆኗም በላይ ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሰች በሙያዋ ምግብ በማብሰልና በትርፍ ጊዜዋም የግለሰብ ቤት ውስጥ ልብስ እጥበት እየሠራች ትገኛለች፡፡ ድርጅቱም በማንኛውም ድግስ ቢኖረው ለእሷ ቅድሚያ በመስጠት ያሠራታል ለሚፈልጉ ሰዎችም በማስተዋወቅና በማገናኘት እረድቷታል፡፡ የወርቄ አማካይ ወርሃዊ ገቢዋ 2800.00 ብር ሲሆን ይህም ለቤት ኪራይ እና ለወርሃዊ ፍጆታ በቂ ገቢ ነው ፡፡ የሚተርፋትንም ብር በድርጅቱ አማካኝነት በከፈተችውየባንክ አካውንት እየቆጠበች ትገኛለች፡፡ አሁን ወርቄ እና ልጇ ሃና እጅግ ደስተኞች ናቸው፡፡ ጤናቸው የተጠበቁ ጠንካራና ባለብሩህ ፊት ሆነዋል፡፡ ወርቄ ከጥገኝነት የተላቀቀች በራሷ የምትተማመን ጠንካራ እናት ሆናለች፡፡ከፊታቸው አስደሳች ድንቅ ሕይወት እንደሚጠብቃቸው ሙሉ ተስፋ አላቸው ፡፡ ድርጅቱም በሆነው ነገር እጅግ ደስተኛ ነው፡፡
እነሱን ለመደገፍ ከእኛ ጋር ለቆማችሁ ሁሉ በእናቶችና በሕፃናት ስም እንዲሁም በፍቅር ስም ከልብ እናመሰግናለን!
ፍቅር ለሕፃናት እና ለእናቶች በጎ አድራጎት ድርጅት